ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ጠንካራ የፋይናንስ አቅሙን፣ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴውን እና ለመልካም የኮርፖሬት አስተዳደሩ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በቅርቡ በቦርዱ የተወሰዱ አስተዳደራዊ ርምጃዎችን በተመለከተ ግልጽነትን ለማጠናከር፣ የባለድርሻ አካላትን እምነት ለማስቀጠልና ትክክለኛ መረጃ ለማድረስ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫውም የዳይሬክተሮች ቦርድ በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣትና የኮርፖሬት አስተዳደር መርሆዎችን በመጠበቅ፣ ከአንዳንድ የአሰራርና የአስተዳደር ክፍተቶች ጋር በተያያዘ ሰፊ የውስጥ ግምገማ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
በግምገማው መሰረት ከዚህ በፊት ከአሰራር ክፍተት ጋር ተያይዞ ባንኩ ላይ የፋይናንስ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩትን የቀድሞው የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ ቦሩ ( ዶ/ር ) ከስራ ማሰናበቱ ይታወቃል ፡፡
የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የዳይሬክተሮች ቦርድ በሐምሌ 2018 ዓ.ምከሥራና ከደሞዝ ከታገዱ 18 የስራ አመራሮችና ሰረተኞች መካከል ብዛታቸው 6 የሚሆኑ የስራ አመራሮችና ሰራቶኞች ማለትም የቀድሞ ቺፍ ሪቴል ባንኪንግ ዘርፍ ም/ስራ አስፈፃሚ ፤ ሶስት የቀድሞ የመምሪያ ዳይሬክተሮች፤አንድ የቀድሞ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪጅ እንዲሁም አንድ የቀድሞ የዲስትሪክት ኦፕሬሽን ዲቪዥን ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ሰራተኞች ላይ የህግ አግባብን ተከትሎ የሥራ ውላቸው እንዲቋረጥ ወስኗል።
ባንኩም ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፍ የአሰራር ስርአትን በመከተልና በህግ አግባብ መሆኑን ለብሔራዊ ባንክ አሳውቋል።
ባንኩ የገጠመውን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ አሁንም በህግ አግባብ እየተከታተለ የሚገኝ ሲሆን÷ እንደ አስፈላጊነቱ በቀጣይ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚሰጥ ተመላክቷል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በቀጣይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ያለውን ገንቢና ሙያዊ የሥራ ግንኙነት በማጠናከር የሚቀጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ሁሉንም ሕጎች፣ ደንቦችና የቁጥጥር መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ለማክበር በቁርጠኛነት እየሰራ ይገኛል።
በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባው ባንኩ የሚሰጠውን አገልግሎት በሁሉም ቅርንጫፎችና የዲጂታል ባንኪንግ አማራጮቹ ፈጣንና አሰተማማኝ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ፡፡
ባንኩ የዲሬክተሮች ቦርዱ በባንኩ ላይ ላሳዩት ቀጣይነት ያለው እምነትና ድጋፍ አመስግኖ በቀጣይም በግልጽነት፣ በተጠያቂነት፣ በታማኝነትና በሙያዊ ብቃት ባንኩን በመምራት አስተማማኝ፣ ዘመናዊ እና ጥራት ያለው የባንክ አገልግሎት መስጠቱን እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡
የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የዲሬክተሮች ቦርድ አዲሱ ዓመት የሰላምና የጤና እንዲሆን እየተመኘ የተጀመረውን የዕድገትና የስኬት ጉዞ በጋራ በማስቀጠል በአብሮነት የሚሰራበት ዘመን እንዲሆን ተመኝቷል፡፡