የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል የሚያደርጉ ተግባራት ይጠናከራሉ -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

September 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክረን እንቀጥላለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያን መርቀው በይፋ ስራ አስጀምረዋል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ፥ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያን ዕድገትና ልማት ሊያስቆሙ የሚሞክሩ ኃይሎችን ከማይችሉት ተራራ ጋር እየታገሉ መሆኑን በተግባር እናሳያቸዋልን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት የተመዘገቡ በርካታ ስኬቶች ለነገዋ ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሚሊየን የሚልቁ ዜጎች ድምፅ በመስጠት ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚመራቸውን መንግሥት የመረጡበት፣ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ አራት ሺህ ዜጎች በጋራ መክረውና ዘክረው የኢትዮጵያን መፃኢ ጊዜ የወሰኑበት፣ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ጠቅላላ ድምሩን 56 ቢሊዮን ማድረስ የተቻለበት ዓመት መሆኑንም አመልክተዋል።

እነዚህ የስምረት የድልና የመከናወን ስኬቶች ተሰናስለው ኢትዮጵያ ከ10 ነጥብ 2 በመቶ በላይ ዕድገት እንድታስመዘግብ አስችሏታል ነው ያሉት።

ሎጂስቲክስ ከትራንስፖርት፣ ወደብ፣ የባቡር መሰረተ ልማት ለአርሶ አደሩ እስከሚደርስ ያለውን ሰንሰለት የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ ዕድገት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

የሎጂስቲክስ አገልግሎት ችግር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አንቆ የቆየ መሆኑን በማንሳት፣ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል እነዚህን ችግሮች እንደሚፈታ አስገንዝበዋል።

የሞጆ የሎጀስቲክስ ማዕከል የኮንቴነር የመያዝ አቅም ከ500 ሺህ ወደ አንድ ሚሊዮን ያሳድጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዕድገት የተሟላ እንዲሆን ሁሉም ማዕዘናትን ከጫፍ ጫፍ ማገናኘት እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።

በ2018 ዓ.ም የብዙ ድል፣ ስኬትና መከናወን ዘመን እንደነበር ገልጸው፤ በ2019 ዓ.ም የላቀ የምንፈፅምበት ዓመት ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።