አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አፈ ጉባዔው በመልዕክታቸው÷ የተፈጥሮ ዑደት የሆነው የዘመን መለወጥ ሰዎች ከትናንት እንዲማሩ እና ነገን በተስፋ ለመገንባት አዲስ ጉዞ እንዲጀምሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብዝኀ ቋንቋዎች፣ ማንነቶች እና እሴቶች ያሸበረቀች ሀገር መሆኗን አውስተው÷ ይህ ብዝኃነት የጋራ ውበት እና ሀብት እንጂ የመለያያ ግንብ እንዳልሆነ አንስተዋል።
መጪው ዓመት የልዩነት ትርክት የሚደርቅበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጸናበት እና በአዲስ ወኔ ወደ ልዕልና የሚሸጋገሩበት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ለመወጣት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ ኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች እንዲሰጡ እና የፌዴራልና ክልሎች የገቢ ክፍፍል ቀመር እንዲሻሻል ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል።
አፈ ጉባዔው አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል።