አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በተከናወነው የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችል ትክክለኛ መሠረት ተጥሏል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።
የትምህርት ሚኒስትሩ እንዳሉት፥ መንግሥት የተሟላ ዜጋ የማፍራት፣ የግብረገብና የእውቀት መለኪያዎችን የማጠናከር እንዲሁም የትምህርት አሰጣጡን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ሰፊ የሪፎርም ስራዎችን ሰርቷል።
የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሰጡ መደረጉ የትምህርት አሰጣጡን እውነተኛ ገጽታ ማሳየት ማስቻሉን ገልጸው በ2018 የትምህርት ዘመን ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች ምጣኔ ወደ 12 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።
ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በልዩ ድጋፍና ክትትል በማስተማር ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻልም ትኩረት መሰጠቱን አንስተው በ2018 የትምህርት ዘመን በቦንጋ፣ በጅግጅጋ፣ በጋምቤላ፣ በወሊሶና ቡኢ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በ2019 የትምህርት ዘመን ደግሞ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ለማሳደግ በአርባ ምንጭ፣ በባህርዳር፣ በድሬዳዋ እና በአሶሳ ተማሪዎችን አወዳድሮ ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ 13 አዳዲስ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የኮምፒውተር ላቦራቶሪዎችን በማስፋፋት፣ የዲጂታል መጽሐፍትንና የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት የማሳደግ ስራ ተከናውኗል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ባለፉት 3 ዓመታት ውስጥ 146 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ሀብት በገንዘብና በዓይነት ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው በዚህም 14 ሺህ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ ሆነው መታደሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 8 ነጥብ 7 ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወደ ራስ ገዝነት ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን እና የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ምደባም በውድድር፣ በእውቀትና በችሎታ ላይ ብቻ በተመሰረተ ግልጽ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
ከተከናወኑት የሥርዓተ-ትምህርት ክለሳዎች፣ የግብረገብና የታሪክ ትምህርቶች መካተት እንዲሁም ከመዋቅራዊ ሪፎርሞች አንጻር ሀገሪቱን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፎች በብቃት ሊመሩ የሚችሉ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችል ትክክለኛ መሠረት ተጥሏል ብለዋል።