አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፥ ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተን በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል። በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በመከላከያ እና ደኅንነት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት እንዲሁም በቴክኖሎጂ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጡበት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም የትምህርት ልምድ ልውውጦችን ማስፋት፣ በባህል እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ዕድሎች ዙሪያ መምከራቸውን ጠቁመዋል። ለኮፕ 32 በሚደረገውን ዝግጅት እና ያለውን አጋርነት ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ እና በልማት ግቦች ዙሪያ ትብብሮችን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸውንም አንስተዋል።
በተጨማሪም በወል ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረቱ የንግድ እና የኢኮኖሚ ልውውጦችን ይበልጥ ለማስፋፋትም በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም ነው ያመለከቱት።