አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም እየተከሰቱ ያሉ የጂኦፖለቲካ ውጥረቶችን ለመፍታት የብሪክስ ሀገራት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል አሉ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት በብሪክስ ላይ ያላቸው እምነት እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በዓለም እየጨመረ የመጣው የጂኦፖለቲካዊ ውጥረትና ባላንጣነት ታዳጊ ሀገራትን ተፅዕኖ ውስጥ እየከተተ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውጥረቶችን ለመፍታት የስብስቡ ሀገራት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በየጊዜው የሚከሰቱ ወረርሽኞች፣ የአየር ንብረት ለውጥና በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ የተከሰተው የአቅርቦት ሰንሰለቶች መስተጓጎል ዓለምን እየፈተኗት ነው ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን ለመካለከል አባል ሀገራቱ የራስ አቅምና ፈጠራን በማሳደግ በዘላቂ ልማት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዓለም ጂኦፖለቲካ ውስጥ እየተስተዋለ የሚገኘው ቴክኖሎጂንና ወሳኝ የተፈጥሮ ማዕድናትን እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም ዝንባሌ የጋራ እድገትን የሚያደናቅፍ ነው ሲሉ አሰጠንቅቀዋል፡፡
ሕንድ የብሪክስ አባል ሀገራትን ራዕይ ትጋራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዓለም አቀፋዊ ጫናዎች የጋራ መፍትሔ ለመስጠት ሀገራቸው የበኩሏን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ