አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕንዷ ኒውዴልሂ በሳምንቱ መጨረሻ የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎችን ተቀብላ 18ኛውን የብሪክስ ጉባዔ በደመቀ ሁኔታ አስተናግዳለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸው በዚሁ ሁነት ላይ ተሳትፈዋል፤ ከመድረኩ ጎን ለጎን ከሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ የትኞቹን የዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚያዊ ድሎችን አሳካች?
የኒውዴልሂው ጉባኤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን፣ ለኢኮኖሚያዊ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት ለስብስቡ አባል ሀገራት ያስገነዘበችበት፤ ለአፍሪካ የፍትሃዊ ውክልናና ተጠቃሚነት ድምጽ የሆነችበት ነው፡፡
በተጨማሪም ከብሪክስ አባልና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር የተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች በአዳዲስና ነባር የትብብር መስኮች ግንኙነቷን ለማሳደግ ያስቻሉ ናቸው፤ ሀገራቱም ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋራቸው መሆኗን በድጋሚ ያረጋገጡበት ሁነት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተ በመድረኩ ላይ ያደረጉት ንግግር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጠራ ምስል የፈጠረ ነው፡፡
የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ ቀዳሚና ወሳኝ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግዙፍ ኢኮኖሚና ብዙ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባህር በርና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አስፈላጊ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን መሻቷን ለመፈጸም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሰላማዊ አካሄድን እንደምትከተልም ግልጽ አድርገዋል፡፡
ብሪክስ ተፅዕኖው የሚጎላው በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ወሳኔ መስጠት ሲችል መሆኑን ጠቁመው፤ ለአባል ሀገራቱ እድገትና የወደፊት እጣ ፋንታ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዚህም መድረኩ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ የተቻለበት ሆኗል።
ብሪክስ ለዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ኢትዮጵያ ብቸኛ የአፍሪካ ዕጩ መሆኗን መቀበሉ እንዲሁም ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን የኮፕ 32 ጉባኤ በሙሉ አቅም እንደሚደግፍ ማረጋገጫ መስጠቱ የዚህ ጉባኤ ስኬቶች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በተቃረበችበት በዚህ ወቅት ብሪክስ ለዚህ ሂደት የሰጠው ድጋፍ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት ነው፡፡
ከዋናው መድረክ ጎን ለጎን የተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድንና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሁም በወታደራዊ የትብብር መስኮች የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ብሪክስ የአፍሪካ የጋራ ጥቅሞችና ፍትሃዊ የውክልና ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲደግፍ በማግባባት በአህጉሪቱ ያላትን የመሪነት ሚና ያጎላችበት መድረክ ነበር፡፡
እነዚህ ውጤቶች ኢትዮጵያ በሕንዷ ኒውዴልሂ ከተሰናዳው የብሪክስ ጉባኤ ካሳካቻቸው በርካታ ዲፕሎማሲያና ኢኮኖሚያዊ ድሎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ