አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች በሕንድ ለሁለት ቀናት ያካሄዱት ጉባዔ መጠናቀቁን ተከትሎ በወቅታዊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መሪዎቹ በመግለጫቸው በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ሀገራት የሚያካሂዱት የንግድ ጦርነት ታዳጊ ሀገራትን የሚጎዳ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከንግድ ዘርፍ ጋር ተያይዞ በሁለትዮሽ ግብይት ሥርዓት ላይ የሚጣሉ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘቡና የተጋነኑ ታሪፎችንም አውግዘዋል፡፡
ብሪክስ ውሳኔ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ውሳኔ ሰጭ እና አስተካካይ መሆኑን ያስገነዘበው የጋራ መግለጫው÷ አንዳንድ ሀገራት በተናጠል የሚያደርጉት የታሪፍ ጭማሪ የሁለትዮሽ ንግድን እንደሚጎዳ አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት ዓለምን ጫና ውስጥ መክተቱን እና ጉዳዩ የብሪክስ አባል ሀገራትን ጭምር እንደሚያሳስብ ጠቅሷል፡፡
ኢራን የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ አባል ሀገራቱ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን እንዲያወግዙ የጠየቀች ሲሆን÷ ብሪክስ ግን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ገለልተኛ አቋም መያዙ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ብሪክስ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በውይይትና በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ጥሪ በማቅረብ ያለ ጸጥታው ም/ቤት እውቅና በሩሲያ ላይ በግል የሚጣለውን ማዕቀብ ኮንኗል፡፡
በአንጻሩ እስራኤል በፍልስጤም ላይ የምታደርገውን መጠነ ሰፊ ጥቃት የብሪክስ አባል ሀገራት በሙሉ ድምጽ መቃወማቸው ነው የተገለጸው፡፡
የእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ በ1967ቱ የድንበር ስምምነት እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መፍትሔ መሠረት እንዲፈታም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ከግጭቶች በተጨማሪ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓትን ማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስና የፖለቲካ ተቋማት ከአግላይነት የጸዳ አሠራር እንዲከተሉ ብሪክስ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
የ11 ሀገራት መሪዎች የተሳተፉበት 18ኛው የብሪክስ ጉባዔ ‘ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት’ በሚል መሪ ሃሳብ በኒው ዴልሒ መስከረም 2 እና 3 ቀን 2019 ዓ.ም. መካሄዱ ይታወቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ