አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት እንዲመደቡ ተወስኗል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩና በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ትምህርታቸውን መቀጠል ባለመቻላቸው መፍትሔ ከጠየቁ ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ÷ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ደህንነታቸው ወደሚጠበቅባቸው ሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት ተመድበው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ማተኮር ያለባቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ መሆኑን ጠቁመው ÷ በቀጣይ ሀገራቸውን የሚረከቡ ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን አብራርተዋል።
ሀገር ማጽናት የሚቻለው የዛሬው ትውልድ ለነገው ትውልድ ማሰብ ሲጀምር ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ያለውን ሁኔታ በመሸሽ ከትግራይ ክልል የወጡ ተማሪዎች በሰላም የመኖርና የመማር መብት እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም እነዚህን የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች በተለያየ መንገድ ማስተናገድና ትምህርታቸውን ያለመስተጓጎል እንዲቀጥሉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ስለሆነም ተማሪዎች ለምዝገባ በአካል ወደ ትምህርት ሚኒስቴር መምጣት ሳይጠበቅባቸው ከዛሬ ማታ ጀምሮ ይፋ በሚደረገው የበየነ መረብ (ኦንላይን) መተግበሪያ በመጠቀም መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
በምዝገባው ወቅትም ተማሪዎች ከዚህ በፊት ይማሩበት የነበረውን ዩኒቨርሲቲ፣ የትምህርት ዘመናቸውን ና የሚማሩበትን የትምህርት መርሐ ግብር በመግለጽ ባሉበት ቦታ ሆነው የዝውውር ፎርሙን በአጭር ግዜ እንዲሞሉ ማሳሰባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡