አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ለዘላቂ ሰላምና የህዝብ አብሮነት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕብር ያሸበረቁ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ውብ መገለጫዎች አብሮነትና አንድነትን በማጎልበት ጉልህ ሚና እየተጫወቱም ይገኛሉ፡፡
ይህም የኢትዮጵያውያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያሸበረቁ ጌጦቻቸውን በመጠቀም የሀገራቸውን ዳር ድንበርና ሉዓላዊ አንድነት በማስከበር ለሺህ ዘመናት ዘልቀዋል።
በኢትዮጵያ የግጭት አፈታት ሥርዓት ለዘመናት የዳበረ እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ ሀገር በቀል እሴቶች በየዘመኑ በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ሀገር ማቆየታቸውን የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ መድረኮች ይገልጻሉ፡፡
የገዳ ሥርዓት፣ ሽምግልና፣ አፊኔና መሰል ሀገር በቀል ኢትዮጵውያን እሴቶችም በዜጎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት በሀገር ግንባታ ሂደት ጉለህ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረትና የፍጡራን እረፍት እንደመሆኑ ግጭት ጥቃት መፈፀም የኢትዮጵያ ባህል ያፈነገጠ በፈጣሪ ዘንድም የተወገዘ ነው።
የመደመር መንግሥት ለሕዝቦች አንድነትና አብሮነት መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት አስደናቂ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
የጋሞ አባቶች የተበሳጩ ሰዎችን በቀጤማ የመመለስ ጥበብ ኢትዮጵያውያን በሀገር ሽማግሌዎች ላይ ያላቸውን አክብሮት እና እምነት የሚያሳይ ነው።
ይህ የማህበረሰብ እሴት የሆነው የጋሞ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ዕርቅ ሥርዓት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ዜጎች በአስተውሎት በመራመድ ችግሮችን በውይይትና በሃሳብ የበላይነት የመፍታት ልምድን ማዳበር እንዳለባቸው ያሳያል።
ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው ሆኖ ነገር ግን በዜጎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን በጋሞ ማህበረሰብ እርቅ ሒደት፣ በገዳ ሥርዓትና እና ሽምግልና ባሉ የማህበረሰብ ግጭት አፈታት ሥርዓቶችና እሴቶች አለመግባባቶች ለሺህ ዘመናት እየተፈቱ ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ዘላቂ ሰላምን እውን ለማድረግ እንዲሁም አብሮነትና ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር ባህላዊ ሃብቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በውጤታማነት የሚያስቀጥሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡