የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ አረንጓዴ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ለመገንባት እየሰራች ነው-አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

September 15, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አረንጓዴ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው አሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ጉባኤ ላይ ነው።

አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ፥ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት አረንጓዴና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የልማት ስትራቴጂን በሀገራዊ የልማት ዕቅዷ ማዕከል አድርጋ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የታዳሽ ኃይል ማስፋፋትና ዝቅተኛ ካርቦን ያለው ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረት የዚሁ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የትራንስፖርት ዘርፉን ከካርቦን ነፃ ለማድረግ የኤሌክትሪክ ሕዝብ ትራንስፖርት፣ የአረንጓዴ ከተሞች ኮሪደር እና የፅዱ አየር ትራንስፖርት ስርዓትን ከታዳሽ ኃይል ጋር የማስተሳሰር ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

እንዲሁም የቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት፣ የዲጂታል አሰራርን መዘርጋት፣ ሁለንተናዊ ስታንዳርዶችን ማዘጋጀት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እየተሰሩ መሆናቸውንና እነዚህም ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ ከቴክኖሎጂ ሸማችነት ወደ ሀገር ውስጥ አቅም ግንባታ በመሸጋገር ቀጣናዊና አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያና አፍሪካ ከኖርዲክ ሀገራት አዎንታዊ ተሞክሮዎችን እንደሚወስዱ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም የአፍሪካ መፍትሔዎች የአህጉሪቱን እውነታና የትራንስፖርት ፍላጎት ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

አፍሪካውያን በጠቅላላው የእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲሳተፉ የሀገር ውስጥ ገጣጣሚዎችንና አምራቾችን ማጠናከር፣ በምርምርና ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት ስርዓቶችን ማስተሳሰር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።