የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያ የመሰከረችው የኢትዮጵያ ሚና በብሪክስ

By sosina alemayehu

September 15, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ቻይና ጽንሰ-ሀሳብነት የተጀመረው ብሪክስ ዛሬ ላይ የአባል ሃገራቱን ቁጥር በማሳደግ የዓለምን የጂኦ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ምህዳር በዲፕሎማሲው መድረክ እየቀየረ ይገኛል።

ኢትዮጵያም ሀገራዊ ብሎም አህጉራዊ ጥቅሟን በላቀ ሁኔታ ለማንጸባረቅና የኢኮኖሚ ትስስሯን ለማስፋት ባደረገችው ጥረት፤ በፈረንጆቹ 2024 በይፋ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗ ይታወቃል።

18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ በሕንድ ኒውዴልሂ በተሳካ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ ሀገራዊና አህጉራዊ ጥቅሞቿን እንዲሁም አቋሟን በብቃት በማንጸባረቅ፤ የዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ተሳትፎዋን የሚደግፉ እና የልማት ትብብሮቿን የሚያጠናክሩ ተግባራትን አከናውናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብሪክስ ጉባዔ ጎን ለጎን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲንን ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር፣ እንዲሁም የደህንነትና ቴክኖሎጂ ትብብርን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በተለይም ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተጠናከረ የመጣውን ሁለገብ ግንኙነት በመገምገም በምግብ ዋስትና፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በታዳጊ ሀገራት የጋራ ልማት አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በዚህ ውይይት ወቅት ፕሬዚዳንት ፑቲን ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2024 ጀምሮ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗን በማስታወስ ሀገሪቱ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ አፍሪካን በመወከልና የታዳጊ ሀገራትን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች በብቃት በማሰማት ረገድ ትልቅ አቅም እያሳየች ነው።

ሩሲያም የኢትዮጵያን ይህንን እያደገ የመጣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተደማጭነት በትክክል እንደምትገነዘብ ፕሬዚዳንት ፑቲን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም በብሪክስ አባልነቷ ማዕቀፍ ውስጥ በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ፍትሃዊነት እንዲሰፍንና የታዳጊ ሀገራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ሀገራዊ አቋሞችን በንቃት በማንጸባረቅ ላይ ትገኛለች።

በዲፕሎማሲው መስክ የሰላም፣ የደህንነት እና የባለብዙ ወገን ትብብር አቀንቃኝ በመሆን ለዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ቁርጠኝነት ጎልቶ ታይቷል።

በኢኮኖሚ ትስስር፣ በምግብ ዋስትና እና በዘላቂ ልማት ዙሪያ ከአባል ሀገራት ጋር ያደረገችውን ተሳትፎ አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የብሪክስን ማዕቀፍ ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን ፕሬዚዳንት ፑቲን በአድናቆት አንስተዋል።

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ሁለገብ ከፍታና በዓለም አቀፍ መድረክ እየተጫወተች ያለውን ወሳኝ ሚና መስክረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የሩሲያ የረጅም ጊዜ እና አስተማማኝ አጋር መሆኗን ገልጸው፤ የሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት በእኩልነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ከብሪክስ ጋር መዋሃድ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች እያመጣች ያለው አበረታች ለውጥ፤ ሀገሪቱ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ከፍታ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

የዓለም ኃያል ሀገራት በተለይም ሩሲያ የኢትዮጵያን አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሚና በትክክል መገንዘባቸውና እንደ አስተማማኝ አጋር መቁጠራቸው፤ ለወደፊቱ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብር ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ያላት ተሳትፎ ይበልጥ እየጠነከረ እንደሚቀጥልና ለታዳጊ ሀገራት ዕድገትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እንደሚሄድ በግልጽ ያሳያል።

በሶስና አለማየሁ