የሀገር ውስጥ ዜና

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሀገር የሚገነቡ ዜጎች የሚፈጠሩባቸው እንዲሆኑ እየተሰራ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

September 15, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ መስኮች ሀገር የሚገነቡ ዜጎች የሚፈጠሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እየተሰራ ነው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፡፡

‎የትምህርት ሚኒስቴር አዲስ ከተመደቡ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መምህራን ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም በኩል የወደፊቱ ሀገር የሚመሩ ዜጎች የሚፈልቁባቸው ተቋማት እንደሚሆኑ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ‎ ‎ትምህርት ቤቶቹ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ፣ በፖለቲካ፣ በፍልስፍናና በሌሎች መስኮች ሀገር የሚገነቡ ሀገር ወዳድ ዜጎች መፍለቂያ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል። ‎ ‎ሁሉንም በእኩል በማገልገል ሀገርን ከችግር ማውጣት የሚችሉ ዜጎች የሚፈጠሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡ ‎ በትምህርት ቤቶቹ የሚማሩት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ መምህራኑም ከተለያዩ አካባቢዎች በችሎታ የተመረጡ ናቸው ብለዋል። ‎ ‎በፍጥነት እየተለወጠች በምትገኘው ዓለም ውስጥ ከጥገኝነት የተላቀቀች ሀገር መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመው፤ በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የተመደቡ መምህራን ተገቢውን እውቀት በማስተላለፍና በስነምግባር የማነጽ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።