የሀገር ውስጥ ዜና

የብሪክስን ተፅዕኖ የሚያጎላው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጉዞ

By tigist gizachew

September 15, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በህንዷ ኒው ዴልሂ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የነበራት ተሳትፎ መልከ ብዙ ስኬት ያስመዘገበችበት ትልቅ ሁነት ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ለመሆን እያደረገችው ያለው ጥረት የብሪክስን ድጋፍ ማግኘቱ ከጉባዔው ጉልህ ውጤቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ስብስቡ የኢትዮጵያ እና የኢራንን የድርጅቱ አባልነት ጥረት በጥብቅ እንደሚደግፍ ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ለዓመታት ሲጓተት የቆየ ሲሆን፤ የመደመር መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች የድርጅቱ አባል ለመሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቃርባለች፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት ያሳለፈቻቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ውሳኔዎች ለአባልነት ጉዞዋ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ይህ አባልነት የኢትዮጵያ ምርቶች ከቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ጋር እንዲተሳሰሩ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት፤ ብሪክስ በዓለም ንግድ ስርዓት ውስጥ ተፅዕኖው እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ በስብስቡ ውስጥ ተፅዕኖዋን ያሳድጋል፡፡

የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚዎችና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ያሉ 11 ሀገራት ስብስብ የሆነው ብሪክስ ዓለም አቀፉን የንግድና የፋይናንስ ሥርዓት ፍትሐዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኘባል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን፤ በዓለም የንግድ ሥርዓት ማሻሻያ ላይ የብሪክስን የመደራደር አቅምና ተፅዕኖ ያጠናክራል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከምስረታ ጀምሮ እያደረገችው ያለው ጠንካራ ተሳትፎ ከዓለም ንግድ ድርጅት አባልነቷ ጋር ሲቀናጅ፤ የብሪክስ ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ መግቢያ በመጠቀም ወደ አፍሪካ ገበያ በቀላሉ እንዲደርሱ በር ይከፍታል።

በቴዎድሮስ ሳህለ