አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም አቅም የሚሆን ሥራ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ። የምሥራቅ ጎጃም ዞን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምግማና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል፡፡ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በዚህ ወቅት÷ አርቆ በማየት ነገን መመልከት፤ ዛሬ ደግሞ ለነገ መዳረሻችን አልቀን መሥራት አለብን ብለዋል። የጋራ አላማ ላይ ለመድረስ ዕቅድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው÷ የታቀደውን የመፈጸም አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂ እንዲለማመዱና ከዕለት ፍጆታ ያለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያመርቱ ዘመናዊ ግብርና ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት
የጤና ተቋማትን፣ ት/ቤቶችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብና ተቋማትን በኃላፊነት መምራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ አለብን፤ ሰው ሳናስተምር ሀገር ማልማት አንችልም ሲሉ ማስገንዘባቸውን አሚኮ ዘግቧል። ሙስና እና ሕገ ወጥነትን መከላከል እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ለዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የጸጥታ ኃይሉን በማገዝ ሰላምን መጠበቅ እና ይበልጥ በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።