አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በህንድ ኒው ዴልሂ የተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ድል ያገኘችበት መድረክ ነው አሉ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፡፡
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ተመራማሪ አዲስ አለማሁ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ ጉባኤው ሲጠናቀቅ በወጣው የጋራ መግለጫ ኢትዮጵያ ሶስት ስትራቴጂክ ድጋፎችን አግኝታለች፡፡
የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እያደረገች ያለውን ጥረትና የድርድር ሂደት የብሪክስ አባል ሀገራት ለመደገፍ መስማማታቸው እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ ድጋፍ ትልቅ ድል መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትን ሙሉ ድጋፍ አግኝታ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ተጨማሪ መቀመጫ ለማግኘት የምታደርገውን ብቸኛ የአፍሪካ እጩነት ብሪክስ በሙሉ ድምፅ የደገፈበት ውሳኔው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ የምታደርገውን ዝግጅት ብሪክስ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ መግለፁ ሌላኛው ስኬት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት የብሪክስ ተወካይ እና ተመራማሪ ሀይማኖት እሸቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የብሪክስ መድረክ ኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿን ያንፀባረቀችበት መድረክ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና የፋይናንስ ውሳኔዎች ላይ የራሷን እና የአፍሪካን ጥቅም በተሻለ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንድታንጸባርቅ እና የባለብዙ ወገን ሥርዓትን እንድታጠናክር ይረዳታል ነው ያሉት።
መድረኩ የውጭ ግንኙነት አማራጮቿን ለማስፋትና ስልታዊ ሚዛኗን ለመጠበቅ እንደሚያስችላት አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን እንድታጠናክር እና የአፍሪካ ድምፅ እና መሪነቷን እንድታሳድግ እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ የንግድ ትስስር እና የገበያ አማራጯን እንድታሰፋ አስችሏታል ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ