አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ጠንካራ መሰረት ያለው የሕልውና ጥያቄ ነው አሉ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር)።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ የባህር በር እጦት በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ እንድትከፍል በማስገደድ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው።
ይህም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የሀገርን ተፈጥሯዊ፣ መልክዓ ምድራዊ፣ ስትራቴጂካዊና ሕጋዊ የባህር በር ባለቤትነት ለማስመለስ ያነሱትን ጥያቄ ምክንያታዊነት ያጎላዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በባሕር ላይ የሎጂስቲክስና ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ጠንካራ አቅም የገነባች ሀገር መሆኗን አንስተው ብቁ የመርከብ ካፒቴኖችና በዳበረ መዋቅር የሚከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያን አቅም የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት የሚያስቆጭ እንደሆነ እና ይህም በባህር ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል።
የባህር በር አለመኖር ኢትዮጵያን በወደብ ኪራይ፣ በሸቀጦች የወጪና ገቢ እንቅስቃሴ መዘገየት በመፍጠርና ቀጥተኛ ተፅዕኖ በማሳደር የኢኮኖሚ ዕድገትን እየጎተተ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።