አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ዝቅተኛ የአደጋ ተጋላጭ የሆነች፥ ደህንነቷ የተጠበቀና የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም ከተማ በመባል ከአፍሪካ ቀዳሚ፤ ከዓለም ሁለተኛ ከተማ ሆና ተቀምጣለች።
የጂኦስፓሻል ኩባንያ አልፋ ጂኦ በዋነኝነት በሦስት መመዘኛዎች የአዲስ አበባ ከተማን የመዘነ ሲሆን አካላዊ የአየር ንብረት ለውጥ፥ አደጋ ተጋላጭነትና ሊገጥሙ ለሚችሉ አደጋዎች አስተዳደርና ፖሊሲ ምላሽ ላይ በማተኮር ነው ምዘናው የተካሄደው።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ የማላመድ ርምጃዎችን ጨምሮ በተቀመጡት መመዘኛዎች ከተማዋ ከ72 ከተሞች ጋር ተወዳድራ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ለዓለም ከተሞች ምሳሌ ሆናለች፡፡
በዓለም የስልጣኔ ቁንጮ የተባሉትን እንደ ፓሪስ እና ለንደን የመሳሰሉት ከተሞች አስከትላ በዓለም ላይ የአየር ንብረት ተጋላጭነት የምትቋቋም ከተማ በሚል ከአሜሪካዋ ቺካጎ ቀጥሎ በቁንጮ ላይ ተቀምጣለች፡
አዲስ አበባ በኮሪደርና የመንዝ ዳርቻ ልማት ያከናወነችው ስራዎች እና የዘረጋቻቸው ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች በዚህ ደረጃ እንድትቀመጥ አስችሏታል፡፡
አዲስ አበባ የዓለም ቀልብ የምትስብ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ብቻ አይደለችም ከምቹነት ባለፈ የአደጋ ተጋላጭነቷ ዝቅተኛ የሆነች፥ ደህንነቷ የተጠበቀ የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም ከተማ ናት ፡፡
በዓለም አቀፉ ተቋም ለከተማዋ የተሰጠው ማረጋገጫ ለፖሊሲ አውጪዎች፤ ኢንቨስተሮችና የመሰረተ ልማት ባለቤቶች የውሳኔ ሀሳቦች ለመስጠት እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡
በዓለም ላይ የሚገኙ ከተሞች ፈጣን የህዝብ ቁጥር ጭማሪን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡
ይህ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት ማደግ አዳዲስ ፍላጎቶችን ይዞ የሚመጣ ሲሆን፤ በዚያው መጠን ደግሞ ከተሞች ለሚፈጠሩ አዳዲስ ፍላጎቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባቸዋል፡፡
በዚህ መርህ የተቃኘው የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝና የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲቸራት እያደረገ ይገኛል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ መሰረት በመዲናዋ በ8 ወንዞች 59 ኪሎ ሚትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ተከናውኗል፡፡
ወንዞችን ማልማት ከመዋብ ባለፈ የወንዞችን መበከል ይከላከላል፣ የጎርፍ አደጋንና የሙቀት መጠን ይቀንሳል፤ ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚያገኙበት እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትንና አዕምሮአቸውን የሚያድሱበትን ዕድል ይፈጥራል።