የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስና ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቀናል – ዩኒቨርሲቲዎች

By sosina alemayehu

September 17, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲሱ ትምህርት ዘመን አዲስ እና ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቀናል አሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችን ለመቀበልና ለማስተናገድ የሚያስችሉ አጠቃላይ የአስተዳደር፣ የአካዳሚክና የመሠረተ ልማት ዝግጅቶችን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ይደነቁ ተስፋዬ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የተማሪዎች የምዝገባ ሒደት ከፊታችን መስከረም 11 እና 12 ቀን 2019 ዓ.ም ይከናወናል፡፡

አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ከከተማው አስተዳደርና ከዩኒቨርሲቲው የተወጣጡ አካላት ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመው÷ ተማሪዎች ከመናኸሪያ ጀምሮ እስከ ግቢ ድረስ ሕጋዊ መለያ በለበሱ በጎ ፈቃደኞች አቀባበል እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እስከ አካዳሚክ መሪዎች በሚደረግ ጥብቅ ክትትል ተማሪዎች በገቡበት የመጀመሪያ ቀን ትምህርት በይፋ እንደሚጀምር አብራርተዋል፡፡

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሐመድ አሕመድ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው አዲስ እና ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ተማሪዎች የሚኖሩባቸው ክፍሎች በአካባቢው ያለውን ሙቀት ለመቋቋም የሚያስችሉ ዘመናዊ የማቀዝቀዣ መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከአካባቢው አሸዋማ ነፋስ ጋር ተያይዞም የካፌቴሪያዎች፣ የዶርሚተሪዎች እና የመማሪያ ክፍሎች የማጽዳትና የመጠገን ሥራዎች በከፍተኛ ማኔጅመንቱና በፕሬዚዳንቱ ተሳትፎ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መምህራን፣ የኮሌጅ ዲኖች እና የዲፓርትመንት ኃላፊዎች ለአካዳሚክ ሥራ ዝግጁ መሆናቸውንና የተማሪዎች የምዝገባ ሥርዓት በየኮሌጆቹና በየትምህርት ክፍሎቹ እንዲከናወን መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው አክለውም ከሎጊያ ከተማ ጀምሮ አውቶቡሶችን በማዘጋጀት ተማሪዎችን የመቀበል ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ አዲስ ከሚመደቡትና ከሪሚዲያል ፕሮግራም ተማሪዎች ውጭ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ዓመት ያሉ ወደ 2 ሺህ 500 የሚጠጉ ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ካሚል ኑረዲን ÷ ዩኒቨርሲቲው ለአዲሱ የትምህርት ዘመን አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

ተቋሙ የትምህርት መስኩን ከመረመረ በኋላ በ2018 ዓ.ም የ6 ኮሌጆችን ሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ማከናወኑንና አምስቱ የትኩረት መስክ ሥርዓተ ትምህርቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የመማሪያ ክፍሎችን ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር ስማርት ስክሪኖች እና አዲስ ወንበሮች ተገጥመው ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

የሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ ያሉት ነባር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጀምረው የሚገኙ ሲሆን÷ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ጥሪን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ምደባውን ማጠናቀቁን ተከትሎ በቀጣይ ቀናት ጥሪ እንደሚደረግ ተመልክቷል።

በሶስና አለማየሁ