አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ቤተሰባዊ አንድነት ለመፍጠር የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ድርሻ ትልቅ ነው አሉ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጡ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች አቀባበል ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት፤ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አንድ የሚያደርጋቸው በርካታ ጉዳዮች አሏቸው።
ስለሆነም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የክልሎቹን የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በህዝቦች መካከል አንድነት በሚፈጥሩ የጋራ እሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው፤ አዎንታዊ ትርክትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በህዝቦች መካከል የሴራ ፖለቲካ ለመዝራት የሚጥሩና ከጥላቻ ለማትረፍ የሚሞክሩ ኃይሎችን አፍራሽ ተልዕኮ በጋራ መታገል ይገባል ነው ያሉት።
ችግሮችን ለመፍታት መደመር ወሳኝ ነው ያሉት ርዕስ መስተዳድሩ፤ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ቤተሰባዊ አንድነት ለመፍጠር የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ እንዳውም አስረድተዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በህዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትና አብሮነት በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ወጣቶችን በአንድ ዓላማ በማሰባሰብ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የትብብር እሴቶችን ለማጠናከር የሚያግዝ ስለመሆኑም ተመላክቷል።
በማስተዋል አሰፋ