የሀገር ውስጥ ዜና

የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ‘ጊፋታ’ በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው

By Hailemaryam Tegegn

September 17, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ‘ጊፋታ’ በሀዋሳ ከተማ በደማቅ ስነስርዓት እየተከበረ ነው፡፡

የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረ/ፕሮፌሰር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ጊፋታ የወላይታ ሕዝብ ወደ አዲስ ዘመን በተስፋ የሚሸጋገርበት በዓል ነው፡፡

ሕዝቡ ለዘመናት በትውልድ ቅብብሎሽ እያስረከበ የመጣው የአብሮነት መገለጫ መሆኑን አውስተው፤ በዓሉ ከሲዳማ ሕዝብ ጋር በጋራ መከበሩ የሁለቱን ሕዝቦች ጉርብትናና ትስስር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በብዝሃነት ውስጥ አንድነትን ማጠናከር የዛሬው ትውልድ ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፥ ሐዋሳ ከተማ የሁሉም መኖሪያ እንደመሆኗ የጊፋታ በዓልን በከተማዋ በጋራ ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሲዳማና ወላይታ በደም የተሳሰረ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ያወሱት ከንቲባው፤ የወላይታ ተወላጆች በከተማዋ ልማትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የሲዳማ እና ወላይታ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሁለቱ ብሔሮች የባህል ቡድን አባላት ተገኝተዋል።

የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ ‘ጊፋታ’ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በማስመዝገብ ለዓለም ካበረከተቻቸው የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

በመለሰ ታደለ