አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ወቅት የአየር ንብረት አፈጻጸም ግምገማ እና የመጪውን የበጋ አየር ጸባይ ትንበያ ይፋ አድርጓል።
በዚህ ወቅትም በተጠናቀቀው የክረምት ወቅት የተመዘገበው የዝናብ ሥርጭት ከቀደመው ትንበያ ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተመላክቷል።
በክረምቱ ወቅት በሰሜን፣ በምሥራቅ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን መመዝገቡ ተጠቁሟል፡፡
በተለይም በሰሜን ወሎ፣ በአፋር ክልል፣ በማዕከላዊና ምሥራቅ ኢትዮጵያ የጎርፍ እና ተያያዥ ክስተቶች መታየታቸው ተጠቅሷል፡፡
በአንጻሩ በምዕራብ ትግራይ እና በምዕራብ አማራ አብዛኞቹ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ ሥርጭት ተመዝግቧል፡፡
ይህ የአየር ንብረት መለዋወጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የኤልኒኖ ክስተት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ሁኔታው ከዚህ ቀደም በ1990 እና በ2008 ዓ.ም ከተከሰቱት የኤልኒኖ ሁኔታዎች ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ተመላክቷል።
በዚህም በዘንድሮው የበጋ ወቅት በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡
በአንጻሩ በመካከለኛውና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ ያልተጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋም ከተቋማት ቅንጅት ባሻገር በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚሰጡ መረጃዎችን መተንተን እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
በዮሐንስ በቀለ