አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 18 ክለቦች የሚሳተፉበት የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር መርሐ ግብር የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ18 ክለቦች መካከል በ7 የተለያዩ ስታዲየሞች ከመስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.መ ጀምሮ የሚደረግ ይሆናል።
በዚህም መሰረት የምድብ ድልድሉ ይፋ የሆነ ሲሆን÷ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዳማ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነጌሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ ቡና ከሸገር ከተማ መስከረም 29 በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሃላባ ከተማ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ በሃላባ ስታዲየም ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
ሃዲያ ሆሳዕና ከባሕር ዳር ከተማ በአቢዬ ኤርሳሞ ስታዲየም የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጋሞ ጨንቻ ከኢትዮጵያ መድህን በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አባያ ካምፓስ ሜዳ የሚደረግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ነው።
ሃዋሳ ከተማ ከመቻል እና ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚደረጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋዎች ናቸው።
ተጠባቂው የሸገር ደርቢ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በሁለተኛው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።
ሊጉ በቀጣይ ሲጀመር ተመልካቾችን ተደራሽ ለማድረግ ጨዋታዎቹን አርብ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ለማድረግ መታቀዱን ተመላክቷል፡፡
በ2019 ዓ.ም ሊጉ በ18 ክለቦች መደረግ የሚጀመር ሲሆን ÷ አራት ክለቦች እንደሚወርዱ እና ሁለት ክለቦች ከከፍተኛ ሊጉ አድገው በ2020 ዓ.ም ሊጉ በ16 ክለቦች እንደሚቀጥል ተገልጿል።