የሀገር ውስጥ ዜና

300 የሚሆኑ የሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን ታጣቂዎች ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ እጃቸውን ሰጡ

By Hailemaryam Tegegn

September 18, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰላም ጠሉና ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በመቃወም ከቡድኑ ጋር ሆነው አለመዋጋትን በመምረጥ 300 የሚጠጉ የህወሓት ታጣቂዎች በተከዜ በኩል ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ምዕራብ ዕዝ እጃቸውን ሰጥተዋል።

የሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን ታጣቂዎች በምዕራብ ግንባር ተከዜ አቅጣጫ ልዩ ቦታው ተከዜ ድልድይ ግራና ቀኝ አቅጣጫ ነው ለዕዙ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡት።

ታጣቂዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ሆኖ የትግራይን ሕዝብ ሲጨፈጭፍ ከነበረው ሻዕቢያ ጋር ፅምዶ በሚል እሳቤ የፈጠሩት ጥምረት ለትግራይ ሕዝብ የማይጠቅምና የሚጎዳ መሆኑን በመገንዘብ በቀጣናው ከሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ጋር ቀደም ብለው በመሠረቱት ግንኙነት በመነጋገር እና መንገድ በማመቻቸት እጅ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በጠብመንጃ ሳይሆን በመነጋገር እና በመግባባት ነው የሚል እምነት ይዘው ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሠራዊት እጅ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።

ታጣቂዎች ከ280 በላይ የነፍሰ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ በርካታ የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ የጦር ሜዳ መነፅርና ልዩ ልዩ ዶክመንቶች ይዘው መግባታቸውን ዕዙ አስታውቋል።

ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ሠላማዊውን የትግራይ ሕዝብ ወጣት በማፈስ ወደ ጦርነት ለመማገድ የሚሠሩ ዘራፊ እና ወርቅ አውጪ የህወሓት አመራሮችን ፍላጎት በመቃወም እጅ የሠጡት የሕገ ወጡ ህወሓት ታጣቂዎች አሁንም ቢሆን አለመግባባቱ ሊፈታ የሚችለው በጥቂት ጨቋኝ የህወሓት አመራሮች ፍላጎት ሳይሆን በመነጋገር ብቻ ነው የሚል ሙሉ እምነት ይዘው እጅ መሥጠታቸውን ጠቁመዋል።

እጅ ከሰጡ የሕገ ወጡ ህወሓት ታጣቂዎች መካከል ከክፍለ ጦር አዛዥ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሻለቃና የሻምበል አመራሮች ይገኙበታል።

ይህ የሚያመላክተው ታጣቂው ሃይል ሳይፈልግ በሕገ ወጡ ህወሓት ሥርዓት አገዛዝ አሥገዳጅነት የሚዋጋ እንደሆነ ዕዙ አስገንዝቧል።

ሕገ ወጡ ህወሓት ከጦርነት አዙሪት የመውጣት ፍላጎት የሌለው ፅምዶ በሚል አካሄድ ህዝቡን አሁንም ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ለመክተት የሚጥር፣የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሠላም የማይመች፣ የቀረበለትን የሠላም አማራጭ የማይቀበልና በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣ ሥለመሆኑ እጅ የሠጡ ታጣቂዎች ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሕገ ወጡ ህወሓት የአገዛዝ ሥርዓት በመጥላትና ሠላምን በመምረጥ እጅ ለመስጠት የሚጠባበቁ በርካታ የትግራይ ወጣቶች አሉ ያሉት ታጣቂዎቹ ፥ የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠልና ሠላም ለማሳጣት ህወሓት ወጣቱን እያስገደደ ሳይፈልግ ለጦርነት እያዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

ተገዶ የገባው የትግራይ ወጣትም ይህን አውቆ እና ተረድቶ ጊዜና ሁኔታው ሲመቻችለት እጅ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ታጣቂዎቹ መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።