የሀገር ውስጥ ዜና

ብሪክስ ኢትዮጵያ ጉልህ ትርጉም የምትሰጣቸው ጉዳዮችን መደገፉ የሃገራችንን የዲፕሎማሲ ስኬት የመሰከረ ነው – ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር)

By emebet sisay

September 18, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሪክስ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ ጉልህ ትርጉም የምትሰጣቸው ጉዳዮችን መደገፉ የሀገራችንን ፈጣን ዕድገትና የዲፕሎማሲ ስኬት ያሳየ ነው አሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር)።

ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ፥ በ18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ የፀደቀው 140 አንቀጾችን የያዘው የብሪክስ የኒው ዴልሂ የአቋም መግለጫ ኢትዮጵያን በሶስት አንቀጾች ላይ በስም በመጥቀስ ድጋፍ የሰጠበት እና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ የታየበት ነው።

 

በዚህም መሰረት አንቀጽ 20፣ አንቀጽ 105 እና አንቀጽ 107 አባል ሃገራቱ ኢትዮጵያን በድጋፍ ያነሷቸው ቁልፍ ክፍሎች ናቸው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ለአካባቢውና ለዓለም አቀፍ ትብብር ያላቸውን ፋይዳ አብራርተዋል።

 

ለሁለት አስርት ዓመታት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ሲደረግ የነበረውን ጥረት እና የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ በመረዳት የድርጅቱ አባልነቷ እንዲደገፍ መደረጉ ሀገራቱ ለጥምረቱ የሚኖረውን አስተዋጽኦ በትክክል ከመረዳታቸው የመነጨ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

ከዚህ ባለፈም የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አባል እንድትሆን መደገፉ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወሰኑ የአቪዬሽን ውሳኔዎችን የማሳለፍ እና የራሷን ዐሻራ የማኖር አቅም እንዲኖራት ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን አስረድተዋል።

 

በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በ2027 የምታካሂደውን የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP32) ለማዘጋጀት የምታደርገውን ጥረት እና ያስመዘገበቻቸውን አጠቃላይ የልማት ለውጦች የሚደግፍ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

 

በአጠቃላይ 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የኢትዮጵያ አቅም ጎልቶ የታየበት እና አመርቂ የዲፕሎማሲ ስራ የተከናወነበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

በእመቤት ሲሳይ