አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጣሊያን በቀይ ባህር የሚንቀሳቀሱ መርከቦቿን ደህንነት ለመጠበቅ በባብ ኢል ማንዳብ የንግድ መስመር የጦር መርከቦቿን ልታሰማራ ነው፡፡
የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ጉይዶ ክሮሴቶ እንዳስታወቁት÷ የሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ የጣሊያን የንግድ መርከቦች ደህንነት ስጋት ውስጥ ገብቷል፡፡
በቀይ ባህር መርከቦች በነጻነት ካልተንቀሳቀሱ የዓለም ኢኮኖሚ ስጋት ውስጥ እንደሚወድቅ ያስጠነቀቁት ሚኒስትሩ÷ ሮም የንግድ መርከቦችን ደህንነት ለመጠበቅ ከአውሮፓ ህብረት የሚመጣውን የጋራ ውሳኔ አትጠብቅም ብለዋል፡፡
የቀይ ባህርን ደህንነት የማስጠበቅ በቂ አቅም አለን ያሉት ሚኒስትሩ÷ በቀጣይ ጊዜያት የንግድ መርከቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ ሮም የባህር ኃይሏን እና የጦር መርከቦቿን በቀይ ባህር እንደምታሰማራ መጠቆማቸን አል ጄዚራ ዘግቧል፡፡
ጣሊያን በቀይ ባህር መስመር ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ከሚያደርጉና ለዚሁ የንግድ መስመር ትልቅ ትኩረት ከሚሰጡ ሀገራት አንዷ ስትሆን፤ ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የምታስገባቸው ምርቶችና የኃይል አቅርቦቶች በዚህ መስመር ያልፋሉ፡፡
ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና የመንን የሚያካልለው ቀይ ባህር ከ12 እስከ 15 በመቶ የሚደርሰው የዓለም የንግድ ግብይት የሚፈጸመበት የባህር መስመር ነው፡፡
የሁቲ አማፂያን ባለፉት ሳምንታት የቀይ ባህርን ጠረፋማ ስፋራዎች እና ስትራቴጂክ ወደቦችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የቀይ ባህር እና የንግድ መርከቦች ደህንነት ስጋት ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ