የሀገር ውስጥ ዜና

የገጠሩ ማህበረሰብ ከአምራችነት ባለፈ ዘመናዊ አኗኗርን ሊኖር ይገባል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

September 20, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርሶ አደሩን ህይወት በማሻሻል ከአምራችነት ባለፈ ዘመናዊ አኗኗርን የገጠሩ ማህበረሰብ ሊኖር ይገባል አሉ ‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)።

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በክልሉ በከፋ ዞን ጨና እና ሺሾንዴ ወረዳ የተገነቡ ሞዴል የገጠር ቤቶችን መርቀው ለነዋሪዎች ቁልፍ አስረክበዋል። ‎ ‎በዚሁ ወቅት ‎ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ፥ የአርሶ አደሩን ህይወት በማሻሻል ከአምራችነት ባለፈ ዘመናዊ አኗኗርን የገጠሩ ማህበረሰብ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

የሞዴል መንደሮች ግንባታንም በማጠናከርና የአርሶ አደሩን አቅም በማሳደግ የገጠሩን የኑሮ ዘይቤ ወደ ዘመናዊ የአኗኗር ስልት መቀየር ይገባል ነው ያሉት።

የከፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው በገጠር ሞዴል መንደሮች የገቡት ነዋሪዎችም ከኑሮ ዘይቤ ባለፈ በአምራችነት ፤ በጤና አጠባበቅ እንዲሁም ልጆችን በማስተማር እና በሌማት ትሩፋት ስራዎችም ውጤታማ በመሆን ሞዴልነታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል። ‎ ለሌሎች አርሷደሮችም ይህንን ሞዴል በመከተል በራሳቸው አቅም ወደ መሰል ዘመናዊ እና ምርታማ አኗኗር መግባት እንዲችሉ ይህ አርአያ መሆኑም ተገልጿል። ‎ ‎በፍሬው አለማየሁ