አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቴምር ምርት የምርምር ስራዎችን በማስፋፋት ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ።
2ኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በዛሬው ዕለት በሰመራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በፌስቲቫሉ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንዳሉት፥ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
የቴምር ምርት የምርምር ስራዎችን በማስፋፋት እና የአርሶ አደሮችን አቅም በመገንባት ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ፌስቲቫሉ ከውጭ ሀገራት የመጡ አምራቾች ኢንቨስተሮች እና ተመራማሪዎች ልምድ ለመቅሰም እንደሚያስችል በመጥቀስ የቴምር ዛፍን ከመትከል ባለፈ የገበያ ትስስርን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራልም ነው ያሉት።
በዚህም የአርሶ አደሮችን ገቢ ማሻሻል ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻልም አመልክተዋል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አምባሳደር አብደላህ ሀሰን አልሻምዚ በበኩላቸው፥ ፌስቲቫሉ እያደገ የመጣውን የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ግንኙነተ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የቴምር ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል አቅም እንዳላት በማንሳት ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለው የቴምር ዘርፍ ኢንቨስትመንትን፣ ፈጠራን እና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ የግብርና ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ/ር) ናቸው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የቴምር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ለ3ቀናት በሚቀጥለው ፌስቲቫሉ ጥናታዊ ፅሁፎች፣ የመስክ ምልከታ እና የቴምር ምርት አውደ ርዕይ ያካተተ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
በሔኖክ ለሜ