የሀገር ውስጥ ዜና

ለመከላከያ ሠራዊት እጅ በመስጠታችን እፎይታ አግኝተናል – እጅ የሰጡ የሕገ ወጡ ህወሓት ታጣቂዎች

By Mikias Ayele

September 20, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመከላከያ ሠራዊቱ የተደረገልን አቀባበልና እንክብካቤ የሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን አመራሮች ከሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ጋር አይገናኝም አሉ ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ እጃቸውን የሰጡ የህወሓት ታጣቂዎች፡፡

ታጣቂዎቹ ለተሃድሶ ሥልጠና በመንግሥት ወደ ተዘጋጀላቸው ስፍራ በመከላከያ ሠራዊት አሸኛኘት በተደረገላቸው ወቅት እንዳሉት÷ ለመከላከያ ሠራዊት እጅ በመስጠታችን እፎይታ ተሰምቶናል፡፡

በመከላከያ ሠራዊቱ የተደረገላቸው እንክብካቤ የሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን አመራሮች ከሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ጋር የማይገናኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እጃችንን ከሰጠን በኋላ በመከላከያ ሠራዊት የተደረገልን እንክብካቤ ከጠበቅነው በላይ ነው ሲሉም ታጣቂዎቹ በሠራዊቱ የተደረገላቸውን አቀባበል አወድሰዋል፡፡

ከሠራዊቱ ባሻገር የአካባቢው ሕዝብ በሠላም እጃቸውን በመስጠታቸውና ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እንዳደረገላቸው ገልጸዋል፡፡

እኛ በሠላም ለመንግሥት እጅ ሰጥተናል ያሉት ታጣቂዎቹ÷ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የቡድኑ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሎጀስቲክስ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል አባይ ታደሰ በበኩላቸው÷ የሕገ ወጡን ህወሓት የጥፋት ሴራ በመገንዘብ ታጣቂዎቹ እጅ ለመስጠት መወሰናቸው ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡

ሌሎች ታጣቂዎችም ከሕገ ወጡ ህወሓት የጥፋት ወጥመድ በውጣት የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ ማቅረባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡