አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአንድ ወገን ብቻ ሳትወሰን ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ኃይሎች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በብልሃት እና በማመጣጠን እየመራች ትገኛለች፡፡
ከአንድ ወገን አለመወገን ዲፕሎማሲ አንድ ሀገር በታላላቅ ኃይላት መካከል ከሚፈጠር የጎራ ክፍፍልና ወታደራዊ ስምምነቶች ራሱን አግልሎ ነፃ የውጭ ፖሊሲ የሚከተልበት ስትራቴጂ ነው።
ይህ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት በርካታ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን÷ ሀገራት በዓለም መድረክ ላይ ነፃነታቸውን ሳያጡ ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ እና ወዳጆቻቸውን እንዲያበዙ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
የመደመር መንግሥት ይህን በመረዳት ከሁሉም የዓለም ጎራዎች ጋር ለሀገራዊ ጥቅም መስራት መቻሉ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከል እና ለሁሉም ወገን ተፈላጊ አጋር እንድትሆን አስችሏታል።
ለአብነት፣ ኢትዮጵያ በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ከአንድ ወገን አለመወገን የዲፕሎማሲ ስልትን የተከተለች ሲሆን÷ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለሁሉም ሀገራት ያላትን አቋም ገልጻለች፡፡
እንደ ውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት መረጃ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢራኑ ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን ጋር ያደረጉት ውይይት ተለዋዋጩን ዓለም ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ የጋራ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ እና ያለመወገን ዲፕሎማሲ ምሳሌ ነው፡፡
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ልዑካን ጋር የጂኦፖለቲካ ውጥረቶችን በተመለከተ ተመሳሳይ ምክክሮችን ማድረጓ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑም ሆነ ከምሥራቁ ዓለም (ለምሳሌ ከቻይና እና ሩሲያ) ጋር ከወገንተኝነት የፀዳ የዲፕሎማሲ ስልትን የተከተለች ሲሆን÷ ይህም እኩል የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የልማት ግንኙነቶችን እንድትመሠርት በር ከፍቶላታል።
በዚህም ኢትዮጵያ በሁሉም የኃይል ጎራዎች ዘንድ ከሚደርሱ ጫናዎች መውጣት ችላለች፤ በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ግጭቶች እና ውጥረቶች ውስጥ ውሳኔ ሰጭ፣ አደራዳሪ እና ተደማጭ ሀገር እንድትሆንም አድርጓል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሃያላን ሀገራት ተጽዕኖ ነፃ በመሆን የራሷን የውስጥ እና የውጭ ፖሊሲ በራሷ ፍላጎት ብቻ እንድትወስን አስችሏታል፡፡
በሚኪያስ አየለ