አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በጠንካራ መሰረት ላይ በማጽናት ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ሁለቱ ሀገራት ጠንካራና እያደገ የመጣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አላቸው፡፡
በተለይም አሁን ላይ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ በሀገራቱ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
መንግሥት የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብና ሀገሪቱ ከውጭ ዓለም ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት እንድትተሳሰር የሚያደርጋቸውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ኤምባሲው እያስተዋወቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን፣ በቂ ታዳሽ የኃይል አቅርቦት፣ ወጣት የሰው ኃይል እና ስትራቴጂክ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳላት በስፋት መከናወኑንም አንስተዋል።
ከተቀረው ዓለም ጋር በተለይም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከፍተኛ ትስስር እንዳላትና ሌሎች ለኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በኤምባሲው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር የተለያዩ ጉባዔዎች ላይ ከመሳተፍ ጀምሮ ከተለያዩ ኢንቨስትሮች ጋር ውይይቶችና ምክክሮች እስከ ማድረግ የዘለቀ ተሳትፎ እንዳለው ተናግረዋል።
በቅርቡ በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተመራው ልዑክ ቡድን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በተካሄደው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ መሳተፉ ይህንን ጥረት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
የንግድ ግንኙነቱ እንዲጠናከር አሁን ላይ ያሉ ገበያዎችን ማጠናከርና አዳዲስ የገበያ እድሎችን ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የቱሪዝም ኃብት በማስተዋወቅና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ወደ ሌሎች ሀገራት ለቱሪዝም የሚሄደውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያም እንዲያቀና ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም መስህቦችና በገበታ ለሀገር የተሰሩትን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥና ሙያዊ ድጋፎችን ለማስፋት የሚያስችሉ የትብብር አድማሶችን የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም መሰል ሥራዎች ተጠናክረው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጽናት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።