አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት በቀይ ባህር እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሦስትዮሽ ምክክር አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ እንዲሁም ከኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኦርሱላ ቮን ደር ለየን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከተባበሩት መንግሥትታ 81ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የተካሄደው ውይይት፤ በተለይም በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ቀጣና ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህም ግጭቶችን ለማስቆም የሚያስችሉ ቀጣናዊ የሰላም ጥረቶችን ለማጠናከር የሚከናወኑ ጥረቶችን በተመለከተ መነጋገራቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ለአፍሪካ ልማት የሚያስፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦትና የአህጉሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያን በሚመለከት መክረዋል፡፡
የሦስትዮሽ ምክክሩ ሌላኛው አጀንዳ የምግብ ዋስትና እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ሲሆን፤ በአፈር ማዳበሪያ ምርትና አቅርቦት እንዲሁም በግብርና ዘርፈች ትብብር ላይ መወያየታቸውን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
ተቋማቱ የሦስትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡