አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ትግራይ ቴሌቪዥን ባሳራጫቸው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ በሚጥሉ መልዕክቶች ታግዷል አለ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፡፡
ባለስልጣኑ ባወጣው መግለጫ በመንግሥት እና በሕወሓት መካከል በፕሬቶሪያ የተፈጸመውን የሰላም ስምምነት ተከተሎ፣ ባለስልጣኑ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ባደረገው ውይይት መሰረት ቀደም ሲል በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ ወደ ሥራ መመለሱን አስታውሷል፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች የሰላም ግንባታና የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሚዲያው ወደ ሕገ መንግሥታዊና ሙያዊ መስመር እንዲመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ቴሌቪዥን በተሰጠው ዕድል ተጠቅሞ እና የሙያ ሥነ-ምግባር አክብሮ አገልግሎት መስጠት ሲገባው፤ የሀገርንና የህዝብን ደህንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ወደ ግጭት የሚገፋፉ እና ጽንፈኝነት የሚያበረታቱ መልእክቶች በተከታታይ ማስተላለፉን አመልክቷል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ፣ ከዛሬ ጀምሮ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን አስታውቋል።
ማንኛውም ዲጂታል፣ የብሮድካስትም ሆነ የሕትመት ሚዲያ የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያው በህገወጥ መንገድ የሚያሰራጫቸውን ይዘቶች አሰራጭቶ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ መሁኑን ጠቁሟል፡፡
ይህንን መመሪያ ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም ሚዲያ ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ህጋዊ እና አስተዳደራዊና ርምጃዎችን እንደሚወስድ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡