አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ የውስጥም የውጪም ፈተናዎችን አስተናግዳለች፤ ነገር ግን እነዚህን ፈተናዎች በፅናት የተሻገረችው በሕዝቧ ሀገር ወዳድነትና አብሮ የመቆም ብርቱ ተግባር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ መቶ ሚሊየን የቁርጥ ቀን ልጆች ያሏት፥ የክንደ ብርቱዎች እናት የሆነችው ኢትዮጵያ በሠፈር ጎረምሳ የምትሰበር ሀገር አይደለችም፡፡
ታሪክ እንደሚነግረን የዓድዋ ጦርነት ከመካሄዱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ገዢዎች እርስ በእርስ ያልተግባቡበት እንዲሁም ሀገር ከሚያስተዳድሩት ጋር ያቃረኗቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያን ሊያጠቃ ጠላት በመጣ ሰዓት በውስጥ የነበሩ ቅራኔዎችና አለመግባባቶችን በይደር አቆይተው፤ ሁሉም በአንድነት ወጥተዋል፤ ጠላትንም ድል ነስተዋል፡፡
ይህ የሚያሳየን የሀገርን ሉዓላዊነት መከበር መሰረቱ አንድነትና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሀገርን ጥቅም ከራስ ማስቀደም መሆኑን ነው፡፡
አባቶቻችን የውስጥ አለመግባባትን ተጠቅመው ሀገርን ወደኋላ ቢተዉና በተናጠል ቢቆሙ እንዲሁም ከጠላት ጋር ቢያብሩ ኖሮ ዛሬ የምናያትን ነፃነቷ የተከበረችና የታፈረች፣ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን አናገኝም ነበር፡፡
ለኢትዮጵያ አሳቢ በሚመስሉ ላይ ሁሉ እምነት ከመጣልና ህብረት ከማድረግ አስቀድሞ እውነተኛ ለሀገር አሳቢነታቸውን መመርመር የተገባ ነው፡፡
በዲፕሎማሲው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል መርህ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት በማድረግ ይጠቀማሉ፤ ነገር ግን ይህ ሀገርን በሚያጠፉና ለውድቀት በሚዳርጉ ጉዳዮች መሆን አይገባውም፡፡
በእውነተኛ ግብ ላይ ያልተመሰረተ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ያላስቀደመ አካሄድ መጨረሻው ሀገርን ለከፋ ጉዳት መዳረግ ይሆናል፡፡
ለዚህም በአብነት እንደ ሊቢያና ሶሪያ ያሉትን ሀገራት ብናነሳ፤ ለሀገር ሉዓላዊነት ዋጋ ከመስጠት አስቀድሞ ነገን ካለማሰብ በተደረገ አካሄድና አሳቢ በመሰሉ አካላት በተደረገ ትብብር ዛሬ የሚገኙበት ላይ ደርሰዋል፡፡
በመሆኑም የጠላት ጠላት ሁሌ ወዳጅ አይሆንም፤ ይልቁንም ተከብሮ የቆየውን ማንነትና አብሮነት ሊያከሽፍና ሊበትን የመጣ ወዳጅ መሳይ ጠላት መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
በቤተልሔም ግርማ