አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ የሰላጤው ሀገራት ንብረት የሆኑ እና በኢራን ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን የኃይል መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት የሚውል የ5 ቢሊየን ዶላር ፈንድ ይፋ አድርጋለች፡፡
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ይፋ ያደረገው የመልሶ ግንባታ ፈንድ የሰላጤው ሀገራት የነዳጅ ማጣሪያዎችን ጨምሮ የኃይል መሠረተ ልማቶቻቸውን መልሰው በመገንባት የኃይል አቅርቦት ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጡ ያስችላል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም ድጋፉ በሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ምክንያት ሀገራቱ የሚደርስባቸውን የኃይል አቅርቦት መስተጓጎል እና ጫና እንዲቀንሱ ያግዛቸዋል ተብሏል፡፡
በተለይም በድጋፉ የትኛው ሀገር መካተት እንዳለበት እንዲሁም የትኞቹ የኃይል መሰረተ ልማቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ውሳኔው የሀገራቱን የነዳጅ እና የኃይል አቅርቦት ደህንነትን ሊያረጋግጥ እንደሚችል ቢገለፅም፣ ነገር ግን በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የኃይል አቅርቦት መስተጓጎል በዘላቂነት ላይፈታ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
መቋጫውን ባላገኘው የኢራን እና አሜሪካ ጦርነት ውስጥ የትራምፕ አስተዳደር ያደረገው ድጋፍ አሜሪካ ከሰላጤው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያጠናክር ይችላል መባሉን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ኢራን የአሜሪካ ጦር ሰፈር በሚገኝባቸው ሀገራት የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን መፈጸሟ ይታወቃል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ፣ኳታር፣የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ጆርዳን፣ ባህሬን እና ኦማን በኢራን ጥቃት በኃይል የመሠረተ ልማቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ሀገራቱ ኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሟን ያወገዙ ሲሆን በተመሳሳይ አሜሪካ የመሠረተ ልማት ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም የሚያስችል የቅደመ ጦርነት ዝግጅት አላደረገችም ሲሉ ቅሬታቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡
በሚኪያስ አየለ