አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የስንዴ ልማት ስኬት በዓይናችን አይተን አረጋግጠናል አሉ አፍሪካውያን ተመራማሪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች።
በአፍሪካ ዘላቂ የስንዴ ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን፣ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት እና ብሔራዊ የዘር ሥርዓቶችን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ዐውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
በዚህ ዐውደ ጥናት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ ተመራማሪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በአሰላ የሚገኘውን የቁሉምሳ የግብርና ምርምር ማዕከልን እና የስንዴ ማሳዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ፥በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የስንዴ ልማት እና የተመዘገበው ውጤት የሚደነቅና ለሌሎች ሃገራትም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ለመቻል ያደረገችው ጥረት ከወሬ ባለፈ በተግባር ማየታቸውንና ይህም ለአፍሪካ ትልቅ ተስፋን የሰነቀ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአፍሪካ በምግብ ራስን ለመቻልና ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት የመንግሥትና የተቋማት የተቀናጀ አሰራር አስፈላጊ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
የቁሉምሳ የምርምር ማዕከል ምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ረገድ ከአርሶ አደሩ ጋር የፈጠረው ጠንካራ ቁርኝት የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።
በታሪኩ ለገሰ