የሀገር ውስጥ ዜና

በአንድ ወር ውስጥ 15 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

By Melaku Gedif

September 23, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 15 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይልተጠቃሚ ሆነዋል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ።

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው።

ኤሌክትሪክን በመላ ኢትዮጵያ ለማዳረስ ሲተገበር በቆየው ፕሮግራም በአንድ ወር ውስጥ 15 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የሃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በአጠቃላይ 5 ሺህ 435 አባዎራዎችና እማወራዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ 48 ነጥብ 4 ኪ.ሜ መካከለኛ መሥመር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

መሥመሩን ደንበኞች ደጃፍ ለማድረስ 162 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መሥመር ዝርጋታ ሥራ የተከናወነ ሲሆን ÷ 34 የተለያየ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮችም ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከሆኑት የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ውስጥ ዘጠኙ ከግሪድና ስድስቱ በፀሐይ ኃይል አማራጭ ተደራሽ የሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡

በ2035 በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።