አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፉ የሚችሉ አኩሪ ባህሎችና እሴቶች ባለቤት ናት፡፡ ባሕል ግዙፍና ረቂቅ ወይም ውጫዊና ውስጣዊ መልክ አለው፡፡
የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በወርሃ መስከረም በአዲስ አበባ በድምቀት የሚከበሩ ውብ የአደባባይ በዓላት ናቸው፡፡
በዓላቱ አንድነትንና ፍቅርን በሚያጸና እንዲሁም ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ነው የሚከበሩት፡፡
በአደባባይ በሚከበሩት ሁለቱ ክብረ በዓላት የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችን ጨምሮ በርካታ ሕዝብ ይታደማል፡፡
እነዚህ ውብ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ከኢትዮጵያ ለዓለም የተበረከቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው።
አዲስ አበባ ምቹ ተደርጋ መገንባቷ በዓላቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደምቀው እንዲከበሩ ትልቅ እድል ፈጥሯል፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባን ብቻ ጠብቃ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚገናኝባት ከተማ አይደለችም፡፡
በዓመት ውስጥ በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት፣ ውብ ኢትዮጵያዊ ባህሎች እሴታቸውን ጠብቀው በታላቅ ድምቀት የሚከበሩባት ከተማ መሆኗን የከንቲባ ጽ/ቤት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በበርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዜጎችም ትጎበኛለች ፤ ይህ የሆነው ደግሞ ከተማዋ በሁሉም መስክ ምቹ መሰረተ ልማት ስለተሟሉላት ነው።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ በከተማዋ የታየው ለውጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ከፍ አድርጓል፤ የአደባባይ በዓላቱ ደግሞ ተጨማሪ ድምቀት ሆነዋል፡፡
በዚህም አዲስ አበባ ዛሬ ከቱሪስት መሸጋገሪያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻ ከተማነት ተቀይራለች።