ዓለምአቀፋዊ ዜና

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጥሪ አቀረቡ

By Mikias Ayele

September 23, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ÷ የዓለምን የፀጥታ እና ደህንነት በሚወሰነው የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ውክልና አለማግኘቷ ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል፡፡

በ1945 የተመሰረተውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ሀገራት በበላይነት እንደሚቆጣጠሩት ጠቁመው የድርጅቱ መስራች የሆኑት አፍሪካውያን ግን ውክልና እንደሌላቸው አብራርተዋል፡፡

15 አባላት ባሉት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አምስት ሀገራት አባል እና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው እንዲሁም ሌሎች 10 መቀመጫዎች ለሁለት ዓመት በሚቆይ የስራ ዘመን የሚመደቡ አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በምክር ቤቱ ውስጥ አፍሪካ የምትሳተፈው በጊዜያዊ ውክልና መሆኑን የጠቆሙት ዋና ፀኃፊው÷ በዚህም አፍሪካ ቋሚ ውክልና ካላቸው ሀገራት እኩል የመወሰን እድል ማግኘት እንዳትችል አድርጓታል ነው ያሉት፡፡

አፍሪካ በህዝብ ቁጥር፣ በፖለቲካ ተፅዕኖ እና በኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት ብታስመዘግብም፣ ኃያላኑ በሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ግን የወሳኝነት ሚና ተነፍጓታል ማለታቸውን ቻናል አፍሪካ ዘግቧል፡፡

አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እና የድምፅ መስጠት መብት እንዲኖራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እና አባል ሀገራት እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

በአፍሪካ ሕብረት የኤዙልዌኒ መግባቢያ ሃሳብ (Ezulwini Consensus) መሠረት አፍሪካ ቢያንስ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች እና ሁለት ተለዋዋጭ ወይንም ጊዜያዊ ወንበሮች ሊኖሯት እንደሚገባ ሕብረቱ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

በሚኪያስ አየለ