የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያዊነት የጋራ ታሪክና የወል ህልውናችን ማሳያ ነው – አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)

By tigist gizachew

September 23, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊነት በበርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች የታነጸ ነው አሉ የታሪክና የባህል ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)።

አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ መጠን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መነሻ የሆነች ልዩ ምድር ናት።

ኢትዮጵያ በሃይማኖታዊ ስብጥሯ የተለያዩ እምነቶች ከጥንት ዘመን ጀምሮ በሰላም አብረው የኖሩባት ሀገር ናት ብለዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ ከመሆኗ ባሻገር፤ ከቁሩ እስከ ሀሩሩ የሚዘልቁ ሁሉንም አይነት የዓለም አቀፍ የአየር ጠባዮችንና የብዝሃ ህይወት ጸጋዎችን በጥቅል አቆራኝታ የያዘች መሆኗን ተናግረዋል።

በሰው ልጅ የእውቀትና የስልጣኔ እድገት ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያሳደረው የራሷ ፊደልና የጽሁፍ ስርዓት ካላቸው ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗ በራሱ ለየት ያደርጋታል ብለዋል፡፡

በየዘመናቱ በንግድ፣ በጦርነት፣ በረሃብ፣ በእውቀት ፍለጋና በስራ አጋጣሚዎች ምክንያት የተካሄዱ የህዝብ ፍልሰቶችና ውህደቶች ኢትዮጵያውያን እጅግ የተጋመዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የታሪክ ግንዛቤና የምርምር አቅጣጫ በብዛት ትኩረት ካደረገበት የፖለቲካና የጦርነት ታሪክ ወጥቶ ወደ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ታሪክ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በታሪካችን ውስጥ ገበያ እና ንግድ የቁስ ወይም የእቃ መለዋወጫ ብቻ ሳይሆን የሃሳብ፣ የባህል፣ የፍቅርና የማህበራዊ ትስስር ዋና አስታራቂ መድረክ ሆኖ ማገልገሉን ገልጸዋል።

በከባድ የጦርነት ወቅት እንኳ ሳይቀር ገበያ የማይቆም እና ማህበረሰቡን የሚያገናኝ ማዕከል እንደነበር በመጠቆም የገበያ ሥርዓትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በጥናት ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባ አብራርተዋል።

በየባህሉ ያሉ ህዝቡን ለዘመናት አስተስስረው ያቆዩ ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቶችንም ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የውጭ ጠላትና ወራሪ ኃይል ሲመጣ ተባብሮ በአንድነት መሰለፍና ለጠላት እጅ አለመስጠት የኢትዮጵያውያን ዋና የታሪክ ምልክት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችንና የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ይቻላል ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት