ቴክ

የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለህዝባዊ አገልግሎቶች መሠረት የሚሆን ምህዳር ፈጥሯል – አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ

By sosina alemayehu

September 24, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለህዝባዊ አገልግሎቶች መሠረት የሚሆን ምህዳር በመገንባት በኩል ፈጣን እድገት አስመዝግቧል አሉ።

ኢትዮጵያ ከ81ኛው የመንግሥታቱ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደ መድረክ በዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት ላይ ያበረከተቻቸውን ስኬቶች የሚያጎላ መድረክ ላይ ተሳትፋለች።

በመድረኩ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ መሥሪያ ቤት እና የተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ልማት ፈንድ በጋራ በመሆን የከፍተኛ አመራሮች ውይይት በማዘጋጀት የኢትዮጵያን የዲጂታል ዘርፍ እድገት አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እንዲሁም የዲጂታል ክፍያዎች እድገት፣ የዲጂታል መታወቂያ ልምድ እና ለህዝባዊ አገልግሎቶች መሠረት የሚሆን ምህዳር በመገንባት በኩል ፈጣን እድገት አስመዝግቧል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት ያለውን ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እና በተለይም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን፣ አካታችነትን እና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለውን አቅም አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ልማት ፈንድ ዋና ፀሀፊ ፕራዲፕ ኩሩኩላሱሪያ በበኩላቸው፤ አነስተኛ እና በማደግ ላይ ያሉ ኢንተርፕራይዞችን ማበርታት የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚያጫውተው ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በኩል ያለውን የፋይናንስ ጥረትም ማበረታታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።