አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ጂቡቲ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጂቡቲ ቆይታቸውም ከፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ ጋር በጂቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታን ይፋ አድርገዋል፡፡
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ግልጽ አቅጣጫ አለው፡፡ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከርና ጎረቤትን ማስቀደም የፖሊሲው ትኩረቶች ናቸው።
ይህ ፖሊሲ በአጋጣሚ የተቀመረ አይደለም። ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አብሮ የማደግ ትልሟ የወለደው ነው።
ኢትዮጵያና ጂቡቲ የሚጋሩት ድንበር ብቻ አይደለም። በርካታ የጂቡቲ ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ ይህም በንግድ፣ በጉዞና በዕለት ተዕለት ግንኙነት ላይ ጠንካራ መስተጋብር እንዲኖር አድርጓል።
ከቋንቋ ባለፈ ግን የጋራ ባህል፣ ተመሳሳይ ማንነትና ተቀራራቢ ሥነ ልቦናዊ እሳቤዎች በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ በዲፕሎማሲ ቋንቋ “ገር ኃይል” (soft power) ተብሎ የሚጠራው፣ በስምምነት ወረቀት ላይ ሊገዛ የማይችል የተፈጥሮ ትስስር ነው።
ሕዝቦች ቋንቋቸውን፣ ምግባቸውን፣ ሙዚቃቸውን ሲጋሩ፣ በመንግሥታት መካከል የሚፈጠር አለመግባባት እንኳ ወደ ጥልቅ ቀውስ የመሸጋገር ዕድሉ ጠባብ ይሆናል። ይህ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ነው፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከመንግሥታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገር ዘላቂ የሚያደርገው።
የጂቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግድ ወሳኝ መስመር ነው፤ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የውጪ ንግድ የሚያልፈው በዚህ ወደብ በኩል ነው። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከቡና ወደ ውጭ መላክ እስከ ነዳጅ ማስገባት በቀጥታ ከጂቡቲ ወደብ አስተማማኝነት ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ነው።
ትስስሩ ግን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም። ጂቡቲ ለመጠጥነት የምትጠቀምበት ውሃ አብዛኛው ከኢትዮጵያ ይነሳል፤ የኢትዮ-ጂቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ በአፍሪካ ካሉ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ተነስቶ ለጂቡቲ ከተማና ለሌሎች ከተሞች የመጠጥ ውሃ ያቀርባል፤ ኢትዮጵያም ይህንን ውሃ ዓመታት በነፃ ለጂቡቲ ስትሰጥ ቆይታለች።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጂቡቲ ትልካለች። እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩት አንድ ነገር ነው፡፡ ይህ ግንኙነት “ኢትዮጵያ የጂቡቲን ወደብ ትጠቀማለች” የሚል ነጠላ ተረክ ሳይሆን፣ ሁለቱም ሀገራት አንዱ ለአንዱ የማይተካ ሀብት የሚሰጡበት፣ በእውነተኛ መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ነው።
ማንነት፣ የንግድ መስመርና የተፈጥሮ ሀብት ልውውጥ ሀገራትን ሲያስተሳስር ውጤቱ ተራ ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ሳይሆን፣ የቀጣናዊ መረጋጋት ስትራቴጂ ማዕከል ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጂቡቲን ሲጎበኙ፣ የሚያድሱት አንድ የንግድ ስምምነት ብቻ አይደለም፤ የሚያጠናክሩት የሁለት ሕዝቦችን የጋራ ወደፊት የያዘ ትስስር ነው፡፡
በቀጣናው ውስጥ አለመረጋጋት እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ የመቀጠሏ ምርጫ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም።
እርሱ ራሱ አንድ ግልጽ መልዕክት አለው፡፡ የመደመር መንግሥት፣ የቀጣናውን የወደፊት እጣ ፈንታ ከግጭት ይልቅ በትብብር፣ ከመገለል ይልቅ በትስስር ለመቅረጽ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ