የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ጅቡቲ ጂኦግራፊያዊ ቅርበት ለሁለቱ ሀገራት የጋራ የኢኮኖሚ ዕድል ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)

By amele Demisew

September 24, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና ጅቡቲ ጂኦግራፊያዊ ቅርበት ለሁለቱ ሀገራት የጋራ የኢኮኖሚ ዕድል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጁቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታን ይፋ አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ፥ የነዳጅ ምርቶችን ከጅቡቲ ዳመርጆግ ወደ ኢትዮጵያ ደወሌ የሚያጓጉዝ 120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር እንደሚገነባ አስታውቀዋል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ ትብብር የሚለማ ሲሆን፣ በሁለቱም ጫፎች የማከማቻ ተርሚናሎች እንደሚኖሩት ተናግረዋል። ይህም ነዳጅን በረጅም ርቀት በቦቴ ለማጓጓዝ የሚወስደውን ጫና በመቀነስ የኮሪደሩን የሎጂስቲክስ ብቃት ለማሻሻል ያለመ ነው ብለዋል። የፕሮጀክቱን ትርጉም ከነዳጅ ማጓጓዣ በላይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፣ ይህ መሠረተ ልማት የሁለቱን ሀገራት የወደፊት ዕድገት፣ ቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ለማጠናከር የሚያግዝ ኢንቨስትመንት ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል። ሁለቱ ሀገራት ምቹ የሆነውን ጂኦግራፊያዊ ቅርበት ወደ ጋራ ብልጽግና መቀየር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል። ኮሪደሩ ጅቡቲን ከሰፊው የኢትዮጵያ ገበያ ጋር፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ከዓለም አቀፍ ንግድ ጋር የሚያገናኝ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁለቱ ሀገራት ይህንን የጋራ አቅም ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅም መቀየር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በአመለወርቅ ደምሰው