የሀገር ውስጥ ዜና

በቀይ ባህር ንግድ ለተሳሰሩት ኢትዮጵያና ጅቡቲ ጠንካራ የሎጅስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)

By sosina alemayehu

September 24, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት የሚገኙ ቁልፍ አጋሮች በመሆናቸው በሁለቱ ሃገሮች መካከል ጠንካራና ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል የንግድና የሎጅስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጁቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታን ይፋ አድርገዋል፡፡ ‎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ፥ የኢትዮጵያና ጅቡቲ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ መጎልበት አለበት ብለዋል።

የትናንት መሠረተ ልማት የነገን ሃገር አቀፍና ቀጣናዊ ርዕይ ብቻውን ሊሸከም እንደማይችልና ወደቦች፣ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር መስመሮች፣ የሞጆ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል፣ የማጠራቀሚያ ተርሚናሎች እና የቧንቧ መስመሮች ተቀናጅተው በአንድነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እነዚህ መሠረተ ልማቶች በአንድነት ሲሰሩ የልማት ጉዞዎች እንደሚያጥሩ፣ ንግድ እንደሚስፋፋ እና አጠቃላይ ቀጣናው ይበልጥ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ አጋርነት በየራሳቸው ስትራቴጂካዊ ጥንካሬዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑንና ሁለቱም ሃገራት ይህንኑ በማዋሃድ በጋራ ማደግ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

የዳንጎቴ ቡድንም ሃብቱን ፣የኢንዱስትሪ ልምዱን ይዞ መምጣቱን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ውጤት እምነትን እንደሚያጎናጽፍ ሁሉ ያለንን ቁርጠኝነት አሁኑኑ ወደ ስራ በመቀየር ሕዝብ ውጤቱን በአይን እንዲያይ ማድረግ ይገባናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሂደቱም ነዳጅ በፍጥነት መድረስ፣ ወጪ መቀነስ፣ ክምችት ማደግ እና ንግድ ይበልጥ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በሶስና አለማየሁ