አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃላይ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ እያስከተለ ይገኛል።
የዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀን “የዲጂታል አጀንዳ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለቱሪዝም አዲስ ቅኝት” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የታዩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ለውጦች እና የወደፊት አቅጣጫዎች በማስመልከት ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት በቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ አማካሪ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንዳሉት፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለዘርፉ ዓይነተ ብዙ ፋይዳ አለው።
በተለይም ለጉዞ ዕቅድና ጥቅል አዘገጃጀት፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቁጥጥር፣ የግል ምርጫዎች ወይም ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የቱሪዝም አገልግሎት፣ የደንበኛ አገልግሎት ድጋፍ፣ በመረጃ የተደገፈ የገበያ ጥናት እና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎች ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የቱሪስቶችን ፍላጎት፣ ምርጫ፣ ባህሪ እና የቀደሙ ተሞክሮዎችን በመተንተን ለእያንዳንዱ ጎብኚ የሚስማሙ የመዳረሻ፣ የሆቴል እና የጉብኝት አማራጮችን ያቀርባል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ቅፅበታዊ ዳታዎችን በማሰባሰብ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በቅጽበት (Real-time) መረጃ በመስጠት ጎብኚዎች የተሻለ ውሳኔ እንዲወስኑ ያግዛል ነው ያሉት።
ቴክኖሎጂው በዘርፉ ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎት እና የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የቱሪስት መስተንግዶ ተቋማት የእንግዶችን ፍላጎት እና የአገልግሎት አጠቃቀም ዘይቤ በደንብ እንዲረዱ በማድረግ እንዲሁም በአገልግሎት ወቅት የሚፈጠሩ ጉድለቶችን በፍጥነት ለመከታተልና ለማረም እንደሚያስችል ገልፀዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለያዩ ቋንቋዎች ለጎብኚዎች መረጃ በመስጠት እንዲሁም እንደ ሰው የሚያናግሩ ‘ቻትቦቶች’ ለቱሪስቶች ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት እንከን የለሽ የጎብኚዎች ተሞክሮ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂው በመረጃ ላይ የተመሰረተ የገበያ ጥናትና ትንበያ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ የጎብኚዎችን መረጃ በመተንተን የቱሪስቶች ፍላጎትና የገበያ አቅጣጫ ምን እንደሚመስል አስቀድሞ በመተንበይ ውጤታማ የብራንዲንግ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ብለዋል።
ቱሪስቶች መዳረሻዎችን በቀላሉ እንዲያገኙና እንዲመርጡ በመርዳት ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አቶ ቴዎድሮስ አብራርተዋል።
በቅርቡ በቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት አዳዲስ የቱሪስት ዲጂታል መረጃ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።
ማዕከላቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመጠቀም ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ጎብኚዎች ስለ መዳረሻዎች፣ ባህሎችና ታሪክ የተደራጀና ጥራት ያለው መረጃ በፈጣኑ ተደራሽ ያደርጋሉ።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ዘመናዊ፣ ፈጣን፣ ፍትሐዊ እና ለአካባቢ ተስማሚ ደረጃ በማሸጋገር የዘርፉን የወደፊት ጉዞ በተሻለ መንገድ እየቀረጸ ይገኛል።
በቴዎድሮስ ሳህለ