አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማት ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ውብ፣ ዘመናዊ እንዲሁም የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ አድርጓል አለ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አማን አሰፋ (ዶ/ር)።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደተናገሩት÷ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የከተሞች ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት።
ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የከተማ ፖሊሲ ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ዘመናዊና ማራኪ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው የሰዎች የመንቀሳቀስ ምቾት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ተደራሽነት፣ ለሥራና ንግድ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት መሟላቱ የዘመናዊ ከተማ ጥራት መለኪያዎች ናቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ከማሻሻል ባለፈ፣ የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በእጅጉ እያፋጠነው እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተጨማሪም አረንጓዴ ስፍራዎችን በማስፋፋት ዜጎች ንጹህ አየርና መዝናኛ እንዲያገኙ ማስቻሉ ከተሞች ውብና ስማርት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ዘመናዊና ስማርት ሲቲ ለማድረግ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ ለሌሎች የክልል ከተሞች አርዓያ መሆን መቻሉንም አስገንዝበዋል።
በዚህም በክልል ከተሞችም ተግባራዊ የተደረገው የኮሪደር ልማት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ የቀየረ፣ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ያደረገ፣ ውበትን የገለጠና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆኑ ያደረገ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የከተማ ኮሪደር ልማት ከተሞችን ውብ፣ ዘመናዊና ለስራ ምቹ በማድረግ አዲስ ሀገራዊ የመሠረተ ልማት ምዕራፍ የከፈተ ድንቅ ስኬት ሲሆን ይህም የብልጽግና ጉዞን ከማፋጠን ባለፈ ለገጠር ኮሪደር ልማት ዘላቂ ትግበራ ጽኑ መሠረት መጣሉንም አብራርተዋል፡፡