ዓለምአቀፋዊ ዜና

የቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ፓኪስታን የጦር አዛዦች በሪያድ ሊገናኙ ነው

By Mikias Ayele

September 25, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ፓኪስታን የጦር አዛዦች ለሁቲዎች እንቅስቃሴ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ምክክር ለማድረግ ዛሬ ምሽት በሪያድ ይገናኛሉ፡፡

የጦር አዛዦቹ የሚገናኙት የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋህራን፣ የቱርኩ አቻቸው ሀካን ፊዳን እና የፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሳቅ ዳር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ነው ተብሏል፡፡

እንደ ሳዑዲ ፕረስ ኤጀንሲ ዘገባ የቱርክ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሳልሹክ ባይራክታራሮግሉ እና የፓኪስታን የጦር አዛዥ  ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ዛሬ ምሽት ሪያድ ይገባሉ፡፡

የጦር አዛዦቹ በመካ ስምምነት መሠረት የየመን ሁቲዎች በሳዑዲ ላይ ለፈፀሙት ጥቃት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ውይይት እና የአጸፋ ዕቅድ ያወጣሉ ነው የተባለው፡፡

ሳዑዲ አረቢያ በመካ ከተማ የተፈፀመውን የድሮን ጥቃት ተከትሎ፣ ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት በመግለፅ ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት ስትዘጋጅ መቆየቷን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የየመን ሁቲዎች በበኩላቸው ÷ በሳዑዲ አረቢያ ላይ የሚያደረጉትን ጥቃት አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀው በዛሬው ዕለት በጂዛን ግዛት በሚገኙ የሳዑዲ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አስታውቀዋል፡፡

የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በጥቃቱ የሳዑዲ የመሳሪያ ክምችቶችን እንዲሁም የማዘዣ እና መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን አውድመናል ብለዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ