የሀገር ውስጥ ዜና

በዩኔስኮ የተመዘገበው የመስቀል ደመራ የዓለም ትልቅ ሀብት ነው – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ

By tigist gizachew

September 26, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ የዓለም ትልቅ ሀብት ነው አሉ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ የመስቀል ደመራን አዲስ አበባ በመገኘት ከኢትዮጵያውያን ጋር አክብረዋል፡፡

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በተቀደሰችው ሀገር ኢትዮጵያ የመስቀል በዓልን ማክበር በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ ነው ያሉት፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ የዓለም ትልቅ ሀብት እንደሆነ አንስተዋል።

ዩኔስኮ ለመስቀል በዓል ዕውቅና መስጠቱና ዓለም እንዲያከብረው ማድረጉ የተለያዩ እና የተነጣጠሉ የዓለም ህዝቦች አንድ እንዲሆኑ መልዕክት ማስተላለፊያ እንዳደረገው እናምናለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ህንድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በማንሳት፤ ሀገራቱ በመልክዓ ምድር የተራራቁ ቢሆንም በብዙ ጉዳይ አንድ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ቤተሰብ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሁለቱ የሃይማኖት ተቋማት ግንኙነትም ታሪካዊ እና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በ1965 ኦሬንታል የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ አስተባባሪነት አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው የቤተክርቲያን ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አስታውሰዋል።

የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት በቀጣዩ ትውልድም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ አረጋግጠዋል።

በአቤል ነዋይ