የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዝቡ የሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣትና የገባነውን ቃል ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንሠራለን – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

By tigist gizachew

September 28, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝቡ በምርጫ የሰጠንን አደራ ለመወጣትና የገባነውን ቃል በትክክል ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንሠራለን አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።

ጨፌ ኦሮሚያ እያካሄደ በሚገኘው 7ኛ የሥራ ዘመን የ2019 ዓመት የመጀመሪያ ጉባዔ አቶ ሽመልስ አብዲሳን በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሕዝቡ የሰጠንን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣትና የገባነውን ቃል ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።

የሕዝብን አደራ በመደመር መንግሥት እሳቤ ለመምራትና ወደ ውጤት ለመቀየር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

አሁን ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል እና አዳዲስ እቅዶችን በመተግበር የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትብብር እንደሚሠራ አመልክተዋል።

በከተማና በገጠር የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

የተጀመረውን ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ የሚያደናቅፉ ችግሮችን ለመፍታት ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አጽንኦት ሰጥተዋል።