አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ታሪካዊ ስህተቶችን በማረም፣ የጋራ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ እና ሁሉንም አሳታፊ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ኋላ የማይቀለበስ፣ ጠንካራና ዲሞክራሲያዊት ሀገርን የመገንባት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
የማይቀለበሰው የኢትዮጵያ ማንነት በየዘመኑ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ ይበልጥ እየጠነከረ እንዲሁም በተጨባጭ መሬት ላይ በሚታዩ እውነታዎች እየተረጋገጠ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን፣ የውስጥ ፈተናዎችን ብታስተናግድም ማንም ሊቀለብሰው ወይም ሊለውጠው የማይችል ትልልቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻለች ሀገር ናት።
የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ ማንነት የመዳከሟ ምክንያት ሳይሆን በአስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ አንድ ላይ ቆማ እንድትሻገር ያደረጋት ጥንካሬዋ ነው።
የታሪክ፣ የጽናት፣ የባህል እና የነፃነት ህያው ተምሳሌት የሆኑት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ይዘዋቸው የዘለቁት የመከባበር እና የአብሮነት እሴቶች የትኛውንም ከፋፋይ ሃሳብ እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ እና የአፍሪካ ቀንድ እምብርት መሆኗ በዓለም መድረክ ላይ የማይናወጥ ስትራቴጂካዊ ሚና እንዲኖራት አድርጓታል።
የተፈጥሮ ጸጋዎቿ፣ ወጣት የሰው ኃይሏ እና በአህጉራዊ መድረኮች ያላት ቀዳሚ ሚና፣ ሀገሪቱ ወደፊት ለምትጓዝበት የብልጽግና መንገድ የማይቀለበስ አቅጣጫ ያስቀመጠላት ነው።
ህዝቦቿም የመደጋገፍ እና አብሮ የመኖር እሴት በማንኛውም ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ ማዕበል የማይበጠስ ጠንካራ ገመድ ሆኖ ተገምዷል።
በተጨማሪም ባላት ሰፊ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ የቴክኖሎጂና የዲጂታል አሰራር እንዲሁም በተግባር የተደገፈ ቁርጠኝነት ያሰበችውን የምታሳካ ታላቅ ሀገር መሆኗን እና የብልጽግና ጉዞዋ የማይቀለበስ መሆኑን ለዓለም እየመሰከሩ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ የማይቀለበሰው የኢትዮጵያ ማንነት በሕዝቦቿ አጥንትና ደም የተቀረጸ፣ በትናንት የድል ታሪክ ላይ ቆሞ የነገውን ብልጽግና የሚያልም ጽኑ እውነት ነው። ያለፈችባቸው የታሪክ እቶኖች ማንነቷን አቅልጠው አላጠፉትም፤ ይልቁንም ይበልጥ አጠንክረውታል።
ኢትዮጵያ ትናንት የነበረች፣ ዛሬ ያለች እና ነገም በማይቀለበስ ታሪካዊና ባህላዊ ማንነቷ ጸንታ የምትኖር የታላቅነት ማሳያ ሀገር ናት።
በትዕግስት ግዛቸው